የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ማህሙድ
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነት እስካላነሳች እና ለሶማሊያ የግዛት አንድነት ማረጋገጫ እስካልሰጠች ድረስ ከአዲስ አበባ ጋር ለሚደረግ ሽምግልና “ቦታ እንደሌላት” ሶማሊያ አስታወቀች።
ሶማሊያ ይህንን አቋሟን ያሳወቀችው የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት ትላንት ረቡዕ ካደረገው ስብሰባ በኋላ ሁለቱ አገራት “ትርጉም ያለው ንግግር” በማድረግ ችግራቸውን እንዲፈቱ መጠየቁን ተከትሎ ዛሬ ሐሙስ ጥር 9/2016 ዓ.ም. ባወጣችው መግለጫ ነው።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. በመሪዎቻቸው መካከል በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ መሠረት ኢትዮጵያ ነጻ አገር መሆኗን ላወጀችው ሶማሊላንድ ዕውቅናን ለመስጠት፣ ሶማሊላንድ በበኩሏ ደግሞ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ለመፍቀድ ስምምነት ደርሰዋል።
ይህም ሶማሊላንድን የግዛቱ አንድ አንድ አካል እንደሆነች የሚገልጸው የሶማሊያ መንግሥት ስምምነቱን አጥብቆ በመቃወም፣ የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚጥስ ድርጊት ነው በማለት በአካባቢው ውጥረት እንዲፈጠር አድርጓል።
የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤቱ በውይይቱ ኢትዮጵያ እና የሰሜን ሶማሊያ ግዛት (ሶማሊላንድ) የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በአዲስ አበባ እና በሞቃዲሾ መካከል የተፈጠረው ውጥረት እንዳሳሰበው አስታውቋል።
ምክር ቤቱ ከውይይቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ የሶማሊያ እና የኢትዮጵያን ጨምሮ የሁሉም የኅብረቱ አባል አገራት “ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና ነጻነት” እንዲጠበቅ “ጠንካራ ቁርጠኝነት እና ድጋፍ” እንዳለው አስታውቋል።
የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ተወካዮች በተገኙበት ውይይቱን ያካሄደው ምክር ቤቱ፤ ሁለቱ አገራት የተፈጠረው ውጥረት ግንኙነታቸውን ሊያበላሽ ከሚችሉ ተጨማሪ ድርጊቶችን ከመፈጸም እና እርምጃዎችን ይፋ ከማድረግ እንዲቆጠቡ ጠይቋል።


Leave a comment